የኢትዮ ቴሌኮም መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር የምክር ቤትና ጠቅላላ ጉባዔውን ከግንቦት 18-20 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በደቡብ ሪጅን ሐዋሳ ከተማ ያካሄደ ሲሆን በዚሁ ጉባዔ ላይ የዋናው መሥሪያ ቤት የዞንና የሪጅን አመራሮች ተሳትፈዋል።
በጠቅላላ ጉባዔና ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አጠቃላይ የማህበሩን የሥራ እንቅስቃሴ ጨምሮ እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም ድረስ ያለው የሶስት ዓመት የውጭና የውስጥ የኦዲት ሪፖርት ለውይይት ቀርቦ አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ የጸደቀ ሲሆን፣ ከተቋሙ ጋር በቀጣይ ሊሰሩ በሚገቡ ሥራዎች ላይ አቅጣጫ መቀመጡ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩልም የተቋሙን ህልውና ማስቀጠል የሁሉም ሠራተኛ ኃላፊነት መሆኑን ግንዛቤ ላይ በመድረስ የተቀመጠውን ተቋማዊ ዕቅድ በማሳካት የማህበሩንም ሆነ አጠቃላይ የተቋሙን ሠራተኞች የሥራ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባ ጉባዔው አፅንኦት በመስጠት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
እንዲሁም የቀጣዩን ጊዜ የውድድር ገበያ በአግባቡ በመረዳት ወቅቱ በሚፈልገው ልክ የሥራ ተነሳሽነትን፣ ለተቋማችን መቆርቆርንና የባለቤትነት ስሜትን ከፍ በማድረግ በዕውቀት፣ በክህሎትና በዲሲፕሊን እራስን በማነፅ ለተቋማችን ፍፁም ታማኝ በመሆንና ተገቢውን አገልግሎት በጥራትና በፍጥነት በማቅረብ ውድድሩን በበላይነት ለመምራት የሚያስችሉ ዕድሎች በእጃችን መኖራቸውን በመገንዘብ ለተፈፃሚነቱ ሁሉም የበኩሉን ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡
መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ አባላትን በኢኮኖሚና በማህበራዊ አገልግሎት እገዛ ከማድረግ አኳያ፡-
• የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን በተለያየ ዙር በመግዛት 7,650 የማህበሩ አባላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣው የኤሌክትሮኖክስ ዕቃዎች የዋጋ ንረት አባላት ተጎጂ እንዳይሆኑ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉ፣
• የማስተርስ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ የማህበሩ አባላት የብድር አቅርቦት በማመቻቸት 2,439 አባላት የማስተርስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻሉ፣ በዚህ በጀት ዓመትም ለ358 የማህበሩ አባላት ብድር መስጠት የተቻለ ሲሆን ይኸው አገልግሎት በቀጣይ ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ፣
• በውጭ ሀገር ሕክምናቸውን ለማድረግ ችግሩ ላጋጠማቸው የማህበሩ አባላት የገንዘብ ድጋፍ መደረጉ፣
• ከተቋማችን በጡረታ ለሚገለሉ የማህበሩ አባላት በደንቡ መሰረት የገንዘብ ድጋፍ መደረጉ፣
• በሕገ ደንቡ መሠረት በዓመቱ ውስጥ ለቀብር ማስፈፀሚያ እንዲሆን ለሟች ቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍና ለሟች የማህበሩ አባላት ለወራሽ ቤተሰብ ክፍያ መፈጸም መቻሉ፣
• በዚሁ በጀት ዓመት ለመከላከያ ሠራዊታችን የ1.5 ሚሊየን ብር ቀጥተኛ ድጋፍ በማህበሩ ሲደረግ በተለያዩ ጣቢያዎች ውስጥ ለነበሩ ተፈናቃይ ዜጎች ደግሞ በዓይነት 1.3 ሚሊየን ብር በማውጣት የተለያዩ ዕቃዎችን በመግዛት በደብረብርሃን እና በአፋር ክልል ካሳጊታ በመገኘት ለተጎጂዎች ድጋፍ መደረጉ፣ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የብር 50,000 ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ከሥራ ለተፈናቀሉ የማህበሩ አባላት ደግሞ የተለያዩ ድጋፎች መደረጉ፣
• በተቋሙ ውስጥ በሥራ ላይ ሆነው ተገቢ ባልሆነ በተለያየ መንገድ ተጠርጥረው ለእስር ተዳርገው ለነበሩ ሠራተኞች ማህበሩ ጠበቃ በማቆም ክርክር በማድረግ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ማስቻሉ እና
• በዓመቱ ውስጥ የተለያዩ ሠራተኞችን ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በአግባቡ ከሚመለከተው ክፍል ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉ የሚሉት በሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱት መካከል ናቸው፡፡
በጉባኤው ላይ የሕገ-ደንብ እና የአሠራር መመሪያ ማሻሻያ በጠቅላላ ጉባዔው የተደረገ ሲሆን የማህበሩን ቀጣይ በጀት ዓመት እቅድና በጀት በማፅደቅ ሊያከናውናቸው የሚገቡ እና አባላትን በኢኮኖሚው ሊደግፉ እንዲሁም ማህበሩን በፋይናንስ አቅም ሊያጠናክሩ የሚችሉ የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች የተመላከቱ ሲሆን ለዚህም ተግባራዊነት የማህበሩ አመራሮች በቁርጠኝነት ሊሰሩበት እንደሚገባ ጉባዔው አሳስቧል ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካዮችና የተለያዩ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በተቀሩት ጥያቄዎችም ላይ በቀጣይ እንደሚሰራባቸው ተጠቅሷል፡፡
በመጨረሻም ለዚህ ጠቅላላ ጉባዔ በስኬት መካሄድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የተቋማችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ ለደቡብ ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አንዲሁም ለመላው የጉባዔው ተሳታፊዎች መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፣ በማህበሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ላይ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ አመራሮችም የዕውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡፡

