ኩባንያችን እያስመዘገበው ያለው እመርታዊ ለውጥ የማኔጅመንቱና የሠራተኛው የተቀናጀና የተናበበ የሥራ አፈፃፀም ውጤት መሆኑን በመግለፅ ውይይቱን ያስጀመሩት የኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ይህን ውጤታማና የስኬት ጉዞ ለማስቀጠል ብሎም የተሻለ እንዲሆን በተለይም ከዚህ በጀት ዓመት ጀምሮ ከሚጠብቀን የውድድር ገበያ አኳያ በማኔጅመንቱና በሠራተኛው መካከል ያለው መናበብና የዓለማ አንድነትን በማጠናከር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለኩባንያችን ቀጣይነት ያለው እድገትና ትርፋማነት ማረጋገጥ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሠራተኛ ማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ካሳሁን ሰቦቃ በማኔጅመንቱና በሠራተኛ ማህበሩ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት በሚመለከት ሰፋ ያለ ገለጻና ማብራሪያ ያደረጉ ሲሆን ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮችን በስፋት አቅርበዋል፡፡ የሠራተኛ ማኅበር አመራር አባላትም ተጨማሪ የመወያያ ነጥቦችን አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከዋና ሥራ አስፈፃሚ በተጨማሪ ሌሎች የኩባንያው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የማህበሩ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ከሠራተኛ ማኅበሩ በተነሱ ነጥቦች ላይ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሁም በሠራተኛ ማኅበሩ መታየት ያለባቸው ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ በስፋት ከተዳሰሱና የጋራ ከተደረጉ ጉዳዮች መካከል በማኔጅመንቱና በሠራተኛ ማኅበሩ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከርና የጋራ የውይይት መድረኮችን ማመቻቸት፣ የሪፎርም ሥራዎችን በሚመለከት ግልፅነት መፍጠርና በትብብር መስራት፣ የሠራተኛውን ምርታማነት ማሳደግ፣ የኩባንያችንን ተወዳዳሪነትና ትርፋማነት ለማሳደግ የወጪ ቅነሳ ፕሮግራምን መተግበር እንዲሁም የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ሰፊ ንቅናቄ መፍጠር የሚሉ ነጥቦች ይገኙበታል፡፡ በመድረኩ በተነሱ ነጥቦች ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግና የጋራ በማድረግ በበጀት ዓመቱ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት ውጤታማ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚያችን የሠራተኛ ማኅበሩ ለኩባንያችን እድገትና ለውጥ እስካሁን ያሳየውን የትብብር መንፈስ በማድነቅ በቀጣይም መላው የኩባንያው ሠራተኛ ለኩባንያው ያለውን የባለቤትነት ስሜት በማዳበር፣ ሥራውን አክብሮ በመስራት፣ ፕሮፌሽናሊዝምን በማጎልበትና በጎ አመለካከትን በማዳበር ውጤታማ እንዲሆን የሠራተኛ ማኅበሩ የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ ኩባንያችን በሁሉም ዘንድ ተመራጭ እንዲሆን የያዝነውን ዓላማ ለማሳካት ሁሉም የኢትዮ ቴሌኮም ቤተሰብ ከምንጊዜውም በላይ ሰፊ ጥረትና ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡