ማህበራችን ሁለት ሚሊየን ብር በመመደብ የእህል ዱቄት፣ አልሚ ምግብ፣ ሴሪፋም እና የመጠጥ ውሃ በመግዛት በቦረና ዞን ዱቡሉቅ ወረዳ ሂጎ ቀበሌ በመገኘት በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡት ወገኖች ድጋፍ አድርጓል፡፡
በያቤሎ ከተማ በነበረው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች የኢትዮ ቴሌኮም መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር ለዜጎች ችግር ለሰጠው ፈጣን ምላሽ እና የችግሩን ጥልቀት በመረዳትና ድጋፉን በትክክል ለተቸገሩ ዜጎች ለማድረስ ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበው፣ ወደፊትም ከኩባንያችን ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጠናከር የሚሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚሁ የድጋፍ ፕሮግራም ላይ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ሰቦቃ የኩባንያው ማህበረሰብ ከተቸገሩ ወገኖች ጎን እንደሆነ በተግበር ማሳየቱን ገልፀዋል፡፡
ማህበሩ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ለተለያዩ የእርዳታ ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን፣ በደብረብርሃን እና በአፋር ለተፈናቃዮች በቀጥታ በስፍራው በመገኘት ድጋፍ ያደረገ መሆኑን በማስታወስ፣ አሁንም የሚጠበቅበትን የማህበራዊ ኃላፊነት ግዴታ ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝና በቦረና ዞን በመገኘት በአግባቡ መወጣቱን የማህበሩ ፕሬዝዳንት አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ይህን የድጋፍ ሥራ ማስተባበር ላይ ለተሳተፉ የማህበሩ አመራር አባላትና ለደቡብ ሪጅን ተወካዮች እንዲሁም ተቋማችን ለማህበሩ ላደረገው የትራንስፖርት አገልግሎት ድጋፍ ከነአሽከርካሪዎቹ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን በማህበሩ ስም ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡