በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ለረዥም ጊዜ አገልግለው በዘላቂ የጡረታ መብት ለተሰናበቱ 63 ወንድና 17 ሴት በድምሩ ለ80 ሠራተኞች የሽኝት ኘሮግራም ተካሄደ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ለጡረታ ተሰናባች ሠራተኞች የምስክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር በዚህ በአፍሪካ ቀዳሚ በሆነውና ለ128 ዓመታት አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው ኩባንያችን ውስጥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኩባንያውንና የኩባንያውን ደንበኞች አገልግለውና ተገልግለው ለዘላቂ የጡረታ መብት በመድረሳቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸው በጡረታ የተሰናበቱ ሠራተኞች በኩባንያው ቆይታቸው ወቅት ኩባንያው ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ የራሳቸውን የማይረሳ መሠረት የጣሉ መሆናቸውን፣ ለኩባንያው እድገት ያደረጉትን አስተዋጽኦ ኩባንያውና የኩባንያው ማህበረሰብ የማይረሳው መሆኑን፣ በቴሌኮም አገልግሎት ሲጠቀሙና ወደ ቴሌኮም መሥሪያ ቤት ሲሄዱ ያገለገልኩበት መሥሪያ ቤቴ በማለት ኩራት ሊሰማቸው እንደሚገባና በቀጣይም ከተቋሙ ጋር መልካም ግንኙነት እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች መሠረታዊ ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ካሣሁን ሰቦቃ ባስተላለፉት መልዕክት በጡረታ የተሰናበቱ እነዚህ ሠራተኞች ተሰልፈውበት በነበረበት የሥራ መስክ ሁሉ የነበራቸውን ቁርጠኝነት፣ ተቆርቋሪነት እንዲሁም ለተቋሙ ያላቸውን ድንቅ ምልከታ አሁን ባለው ትውልድ ቅብብሎሽ ተደርጎ ኩባንያው አሁን ወደ ደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ደረጃ ማደጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ይህን መልካም ተሞክሮ በወጣቶች በማሻሻል ወጣቶች በአደራ የተረከቡትን ተቋም የበለጠ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያደርሱት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ማህበሩም ቀደም ሲል የነበረውን የድጋፍ አሠጣጥ ከፍ በማድረግ አባላት በጡረታ ከተቋማችን ሲሰናበቱ የሚሰጠውን ድጎማ በማሻሻል በቆይታቸው ልክ የሚከፈል ሆኖ በአማካይ እስከ 35,000 ብር ድረስ እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ወደፊትም ከተቋሙ ሊገኙ የሚገቡ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ላይ ከአመራሩ ጋር ውይይት እያደረገ በየትኛውም መስክ ለመደገፍና አብሮ ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡